Membership Application Form

Personal Information

Professional Information

Membership Type

Declaration

I hereby declare that the information provided is true and correct to the best of my knowledge. I agree to abide by the values and regulations of EMLPA.

የአክሱም ሙስሊም ሴት ተማሪዎች የሂጃብ ክልከላና ሌሎች የትምህርት ተደራሽነትን ለሙስሊሙ ማህበረሰብ የሚገቱ መመሪያና አሰራሮችን ለመከላከል ሊወሰዱ የሚገባቸው የህግ እርምጃዎችን ለመለየት የተዘጋጀ የስልታዊ ሙግት መነሻ ሀሳብና የበጎ ፍቃደኛ ባለሙያዎች ጥሪመግቢያ

  • Home
  • News
  • የአክሱም ሙስሊም ሴት ተማሪዎች የሂጃብ ክልከላና ሌሎች የትምህርት ተደራሽነትን ለሙስሊሙ ማህበረሰብ የሚገቱ መመሪያና አሰራሮችን ለመከላከል ሊወሰዱ የሚገባቸው የህግ እርምጃዎችን ለመለየት የተዘጋጀ የስልታዊ ሙግት መነሻ ሀሳብና የበጎ ፍቃደኛ ባለሙያዎች ጥሪመግቢያ

በርዕሱ ለመግለጽ እንደተሞከረው ለዚህ እቅድና መርሀ-ግብር ዝግጅት መነሻ የሆነው ከህዳር ወር 2017 ጀምሮ ሀይማኖታዊ ግዴታቸው የሆነውን ሂጃብ በመልበሳቸው ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው በተፈናቀሉ የአክሱም ከተማ ሙሰሊም ሴት ተማሪዎች ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው የሚመለሱበትና ለወደፊቱም ሂጃባቸውን ለመተው የሚያስገድዳቸው እንዳይኖር የተጀመሩ የህግ ሂደቶች በበቂ ዝግጅትና የተቀናጀ አሰራር ባለመከናወናቸው እስከ አሁን ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ የነዚህ ከ159 ያላነሱ ተማሪዎች መብት ጥሰት እንዲቆም በህግ አስገዳጅነት ለማስወሰንና ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ የችግሩ መንስዔ የሆኑ መመሪያዎችና አሰራሮች እንዲሻሻሉ የሚያስገድድ ስልታዊ ሙግት ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል፡፡ በመሆኑም ይህ ሰነድ የተዘጋጀው የዚህ ስልታዊ ሙግት አቀራረብና ይዘት ምን መምሰል እንዳለበት በመጠቆም በውይይት ዳብሮ ወደ ስራ እንዲገባ ለማስቻል ነው፡፡       

ከሂጃብ ክልከላና የትምህርት ተደራሽነት ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መነሳት ያለበት ጥያቄና መቅረብ ያለበት ስልታዊ ሙግት አንድ ብቻ እንዳልሆነ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ከነዚህ መካከል በጥቂቱ ለመግለጽ ያክል፡-

  • በተለያዩ የትምህርት ተቋማት በየጊዜው የሚፈጸሙ ድንገተኛ የሂጃብ ክልከላዎች፣
  • በሰላት ምክንያት ከየትምህርት ተቋማቱ የሚባረሩና የሚታሰሩ ተማሪዎች፣
  • በግልጽ መመሪያ የኒቃብ ክልከላ ያለ መሆኑ፣
  • የትምህርት ሚኒስቴር ሙስሊም በዝ በሆኑ ክልሎች፣ ዞኖችና ክፍለ ከተማዎች የሚያቋቁማቸውና ሙስሊም አናሳ (ክርስቲያን በዝ) በሆኑ ክልሎች፣ ዞኖችና ክ/ከተማዎች የከፈታቸው ነጻ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚሰጥባቸው የመንግስት ትምህርት ቤቶች ብዛትና ጥራት ልዩነት እና
  • በየጊዜው በራሱ በትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ መመሪያዎችንና የሚወሰዱ እርምጃዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡    

ምንም እንኳን እነዚህ አድሏዊ አሰራሮችና ጭቆናዎች አንዱ ከሌላው ጋር የማይገናኙ ቢያስመስላቸውም ጉዳዩን በአጽንዖት ለተመለከተውና የሀገራችንን ሙስሊም ጠል አወቃቀርና ታሪክ ለሚረዳ ባለሙያ ግን የተቀናጀ ሙሰሊሙን ማህበረሰብ ከትምህርት ስርዓቱ የማግለል እቅድና ተግባር መሆኑን መረዳት አያዳግትም፡፡ ስለዚህ እንደ ሙሰሊሙ ማህረሰብ የመብት ተቆርቋሪነታችን እነዚህን የመብት ጥሰቶች ለመታገል የአክሱም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ይመለሱ የሚለው ጥያቄ ብቻ እጅጉን አናሳ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ወቅት በዚህ ጉዳይ ላይ ማንሳት የሚገባንን የሙግት ምክንያቶች በሙሉ በአንድ ላይ ማቅረቡ ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለው የሚገኙ ተማሪዎች ጉዳይ አፋጣኝ እልባት እንዳያገኝ ስለሚያደርግና አንዳንዶቹ ጥያቄዎችም ከመቅረባቸው በፊት ሰፊ ጥናትና የመረጃ ማሰባሰብ ስራ ሊከናወንባቸው ስለሚገባ ሙግቶቻችንን ነጣጥለን አፋጣኝ መፍትሄና ዘላቂ መፍትሔ የምንጥይቅባቸውን ጉዳዮች ለይተን ማቅረብ ይኖርብናል፡፡ ከዚህ አንጻር ልናቀርባቸው የሚገባንና የምንችላቸውን የሙግት ዓይነቶች መለየትና መችና በማን ላይ ሊቀርቡ እንደሚገባ በቅድሚያ መለየት ያስፈልጋል፡፡ 

  1. ልናቀርባቸው የሚገባቸውና የምንችላቸው የሙግት ዓይነቶች
    1. የመጀመሪያውና በአፋጣኝ መጀመር ያለበት ክስ፤

ሀ. የአክሱም ሴት ተማሪዎችን በአፋጣኝ ወደ ትምህርት ገበታቸው ሂጃባቸውን ለብሰው የመመለስ መብታቸው ህገ መንግስታዊና ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ቃልኪዳን ሰነዶች የተረጋገጠ በመሆኑ በመመሪያም ሆነ በአሰራር ሊከለከል አይገባም ተብሎ ለማስወሰን የሚቀርብ ክስ መጀመርና መዝገቡ ተመርምሮ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው ሂጃብ ለብሰው እንዳይገቡ የተላለፈው የርዕሳነ መምህራን ትዕዛዛ ላይ እግድ መጠየቅ፡፡

  • ወይም ክሱ እስኪጀመር ድረስ የቅድመ ክስ የእግድ አቤቱታ አቅርበን ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው ሂጃብ ለብሰው እንዳይገቡ የተላለፈው የርዕሳነ መምህራን ትዕዛዛ ላይ እግድ መጠየቅ፡፡

ለ. ይህ ክስም ሆነ አቤቱታ መቅረብ ያለበት በየትምህርት ቤቶቹ ርዕሳነ መምህራን ላይና በትምህርት ቤቶቹ ላይ ብቻ መሆን የነበረበት ቢሆንም የክልል ትምህርት ቢሮው ርዕሳነ መምህራኑን የሚደግፍ መመሪያ ከዚህ በፊት አውጥቶ ይሁን አይሁን መረጃው ስለሌለን አውጥቶ እንኳን ቢሆን ርዕሳነ መምህራኑ በመመሪያ መሰረት ነው የሰራነው ብለው እንዳያመልጡ የወረዳውና የክልሉ ትምህርት ቢሮም በተጨማሪ ተከሳሽ ቢደረጉ የተሻለ ነው፡

1.2   ከዚህ በላይ በቀረው ክስ ዓይነት የሚገኘው ውጤትና የሚሰጠው ፍርድ አንድ ጉዳይ ላይ ብቻ ሊሆን ስለሚችልና በክርክሩ ወቅትም የክልሉ ትምህርት ቢሮ የ1995 መመሪያ መሰረት የራሴን አሰራርና መመሪያ አውጥቻለሁ የሚል ቢሆንም እንኳን መሰል መመሪያዎች ህገ መንግስቱንና ዓለም ዓቀፍ ሰብዓዊ መብት ቃል ኪዳን ሰነዶችን የሚጻረር በመሆኑ እንዲሰረዝና አሰራርም ካለ እንዲቆም ለማስወሰን የሚቀርብ ክስ ነው፡፡

  • ከዚህ ክስ ጋር በተያያዘ ተከሳሽ የሚሆኑት ተፈጻሚነት እንዳለው መመሪያና ወይም አፈጻጸም መሰረት የወረዳውንና የክልሉን ትምህርት ቢሮ ብቻ ሊሆኑ ይችላል፡፡
  • ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት የ1995 መመሪያ ሳይሆን ተፈጻሚነት ያለው የ2000 መመሪያ ነው ከተባለ በዚሁ ክስ ላይ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴርንም በተከሳሽነት ማካተት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡
    • የትምህርት ሚኒስቴር በጠቅላላው በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ ለሚፈጸሙ አድሏዊና ኢ-ህገመንግስታዊ መመሪያዎችና አሰራሮች የከፈታቸው በሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲዘጉ የሚያደርግ ሰፊና ጥናት ላይ የተመሰረት የስልታዊ ሙግት ክስ፡፡ በዚህ ሙግት ስር ሁለት ዓይነት ክሶች ሊቀርቦ ይችላሉ፡፡

ሀ. አንደኛው ክስ በጠባቡ አሁን በስራ ላይ ያሉ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተያያዙ ህግ፣ ደንብ፣ መመሪያና አሰራሮች ውስጥ አድሏዊ የምንላቸውን (ለአድሏዊ አሰራርና መመሪያ በር ይከፍታሉ የምንላቸውን) መርጠን እንዲሻሩልንና በሌላ ህገ መንግስታዊና ዓለማ አቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶቻችን መከበራቸውን በሚያረጋግጡ ህግ፣ ደንብ፣ መመሪያና አሰራር እንዲቀየሩ ለመጠየቅ የሚቀርብ ክስ፡፡

ለ. ሁለተኛው ክስ ደግሞ ሰፋ ተደርጎ በጠቅላላው ከሀገራችን ዘመናዊ ትምህርት ዘውዳዊና ክርክቲያናዊ መሰረቶች ጀምሮ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ያወጣቸውን፣ መመሪያዎች፣ አወቃቀሩን፣ አሰራሩን፣ የሰራተኞች የሀይማኖትና ሌሎች አደረጃጀቶች አካታችነትና ስብጥር እንዲሁም በጠቅላላው ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር ያለውን ትራክ ሪከርድ እስከ መመርመር የሚደርስ ጥናት በማከናወን ተቋሙ እራሱን ገምግሞ የእርምት እርምጃዎችን እንዲወስድ እስከመጠየቅ የሚደርስ ጥናት ላይ የተመሰረት ስልታዊ ሙግት ማቅረብ ነው፡፡

  • በተከሳሽነት ሊካተቱ የሚገባቸው ተቋማት እና የመንግስት ባለስልጣናት

በክሱ ውስጥ ተከሳሽ ተቋማት እነ ማን ይሁኑ?

በዚህ ረገድ ዋነኛው የመለያ መለኪያችን የሙስሊም ሴት ተማሪዎች እስላማዊ አለባበስ በትምህርት ተቋማት በተለያየ ደረጃ ክልከላ በማድረግ ረገድ፡-

ሀ. የፖሊሲ ሀሳብ አመንጪ በመሆን የሚሳተፉ ተቋማት

  1. የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር

በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 የፌደራል መንግስቱ አስፈጻሚ አካላት ስልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ሲሆን፣ በአንቀጽ 34 ስር የትምህርት ሚኒስቴር ስልጣንና ተግባር ተደንግጎ ይገኛል፡፡

1/ በዚሁ መሰረት በአንቀጽ 34/1(ሀ) የአጠቃላይ እና የከፍተኛ ትምህርት፣ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎች፣ ሕጎች እና ፕሮግራሞች ያመነጫል፣ ለአፈጻጸሙ ከሀገራዊ የልማት አቅጣጫ ጋር የተጣጣመ ዝርዝር መርሀ ግብር ያዘጋጃል በሚመለከተው አካል ሲጸድቅም ተግባራዊ ያደርጋል፡፡

ይህ ድንጋጌ በግልጽ እንደሚያሳየው የአጠቃላይ እና የከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲዎችን እና ህጎችን የሚያመነጨው ትምህርት ሚኒስቴር ሲሆን የትምህርት ፖሊሲ ሲመነጭ ከአድሎ የጸዳ እና ሁሉንም አካታች መሆን ሲገባው የሙስሊም ሴት ተማሪዎች ኢስላማዊ አለባበስን መሰረት በማድረግ ሙስሊም ሴቶች ከትምህርት እንዲገለሉ በማድረግ ረገድ እንደ ፖሊሲ አመንጪነት ትምህርት ሚኒስቴር ተጠያቂ ይሆናል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የሂጃብ (የሙስሊም ሴት ተማሪዎች ኢስላማዊ አለባበስ) ክልከላ እንደ ፖሊሲ ቀርጸን አልተንቀሳቀስንም ወይም ፖሊሲያችን ውስጥ የለም የሚል ሀሳብ ሊነሳ ይችላል፤ ነገር ግን ፖሊሲው መሰል ክልከላዎች እንዲቀሩና አድሎን የሚያስቀር እስካልሆነ ድረስ የሂጃብ ክልከላውን የፖሊሲ ድጋፍ እንዳለው ሊቆጠር ይችላል፡፡ በተጨማሪም ህግ መሰረቱ ፖሊሲ ነው፤ በመሆኑም ሂጃብ ከልካይ የሆነ ህግ ትምህርት ሚኒስቴር ሲያመነጭ እና ህጉ እንዲወጣ ሲያደርግ ክልከላው የፖሊሲ መሰረት እንዳለው በግልጽ ያስረዳል፡፡ ስለዚህ ትምህርት ሚኒስቴር ሂጃብን መከልከል የሚያበረታታ ፖሊሲ በማመንጨት፣ በማጸደቅ እና በመተግበር ወይም ከአድሎ የጸዳ የትምህርት ፖሊሲ ባለማመንጨትና ተግባራዊ ባለማድረግ በመብት ጥሰቱ ዋነኛው ተሳታፊ ነው፡፡

2/ በተመሳሳይ መልኩ ከላይ በተገለጸው አንቀጽ 34/1(ሀ) ስር ትምህርት ሚኒስቴር ህጎችን እንደሚያመነጭ ተደንግጓል፡፡ በዚሁ መሰረት ይህንን ሂጃብ ከልካይ የሆነውን ህግ እንዲመነጭ ያደረገው ትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን የህግ ሽፋን ተሰጥቶ በሚደረግ የመብት ጥሰት ላይ ትልቅ ተሳትፎ ያለው ትምህርት ሚኒስቴር ስለሆነ ተከሳሽ መሆን ይኖርበታል፡፡

  • የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁ. 1152/2011 አንቀጽ 38/1(ሠ) ስር የተማሪዎች መብቶች ሲደነግግ ’ተማሪዎች ማንኛውም አይነት አድሎ ወይም ትንኮሳ እንዳይደርስባቸው ህጋዊ ከለላን የማግኘት መብት አላቸው ይላል፡፡’

በሀይማኖታቸው ምክንያት አድሎ (Discrimination) እየተፈጸመባቸው እና ከትምህርት ገበታቸው እንዲፈናቀሉ እየተደረገ ሲሆን ይህ ከአግላይነት ነጻ የመሆን መብት የተደነገገው በራሱ በትምህርት ሚኒስቴር አመንጪነት ወጥቶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀ ህግ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሂጃብ ለመከልከል የወጣው መመሪያ ከህገ-መንግስቱ፣ ከአለም አቀፍ ቃልኪዳኖችና ስምምነቶች እንዲሁም ከላይ ከተጠቀሰው አዋጅ ጋር የሚቃረን ነው፡፡

በመሆኑም የትምህርት ሚኒስቴር አድሎ ሚከለክል ግልጽ አዋጅ ታውጆ እያለ ሂጃብ ከልካይ የሆነ ከ2004-2007 በነበረው የድምጻችን ይሰማ ሀገር አቀፍ ሰላማዊ ትግል ምክንያት ትግሉን በመፍራት ግብታዊነት በተመላው መልኩ የወቅቱ አገዛዝ ሂጃብን የሚከለክል መመሪያ እንዲወጣ በማድረግ ተግባራዊ ማድረጉ ሳያንስ አሁንም በተነጻጻሪነት አድሎን የሚከለክል አዋጅ ታውጆም ከልካዩ መመሪያ ተግባራዊ ማድረጉ ለመብቱ መጣስ ትምህርት ሚኒስቴሩ አስተዋጽዖ ማድረጉ የሚያሳይ ነው፡፡

  • አንዳንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት(ዩኒቨርሲቲዎች)

ከአዋጅ ቁጥር 1152/2011 አንጻር ተማሪዎች ከየትኛውም አይነት አድሎ ነጻ የመሆን ህጋዊ ከለላን የሚሰጥ አዋጅ ታውጆ እያለ ሂጃብ ከልካይ የሆነ መመሪያ መሰረት በማድረግ ሙስሊም ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው የሚያፈናቅሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወይም ዩኒቨርሲቲዎች በተለይ ዲላ ዩኒቨርሲቲ እና መሰል ጥሰት የሚያካሄዱ ዩኒቨርሲቲዎች ተከሳሽ ቢሆኑ ጥሩ ነው፡፡

  • የክልልና የከተማ መስተዳድር ትምህርት ቢሮዎች

 በአብዛኛው ክልሎች ትምህርት ሚኒስቴር የሚቀርጻቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም ህጎችን ተግባራዊ የሚያደርጉ ሲሆኑ በአንዳንድ ክልሎች ደግሞ ሂጃብን የሚከልክል መመሪያ በማውጣትና በመተግበር የሚሳተፉ ቢሮዎች እና በየዕርከኑ ያሉ መዋቅሮቻቸው ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል፡፡

በዚህ ረገድ ዋነኛው ተጠቃሹ ክልል ትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ሲሆን ሂጃብ ከልካይ መመሪያ በማውጣት (1995) እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ማለትም የአክሱም ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት መመሪያውን በመዘርጋት በአክሱም ከተማ ያሉ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዲገለሉ በማድረግ በመብት ጥሰቱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

ስለዚህ እንደ ተቋም ትምህርት ቢሮው ኢ-ህገመንግስታዊ ህግ በማውጣት እንዲሁም የታችኛው የትምህርት መዋቅር ህገ-ወጥ የሆነ ተግባር ሲተገብር ቢሮው ምንም የዕርምት እርምጃ አለመውሰዱ ተጠያቂ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም በትግራይ ክልል በተደረገው የሂጃብ ክልከላ ከቢሮው እስከ ታችኛው መዋቅር ማለትም እስከ ትምህርት ቤቱ ድረስ እንደ ተቋም ተከሳሾች ሊሆኑ ይገባል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የሚሳተፉ የክልል ትምህርት ቢሮዎች እና መዋቅሮቻቸው ተከሳሽ ሊደረጉ ይገባል፡፡ በአጠቃላይ የሂጃብ ክልከላ መመሪያ በማውጣት የሚከለክሉ እንዲሁም በፌደራል ደረጃ የወጣውን ሂጃብ ከልካይ መመሪያ በባለቤትነት ወስደው የሚያስፈጽሙ የክልል ትምህርት ቢሮዎች እና መዋቅሮቻቸው በተለይ ጥሰቱ ያለበት ቦታ በአግባቡ ተለይተው ተከሳሽ ቢደረጉ ጥሩ ነው የሚል እምነት አለን፡፡

ለ. በስልታዊ ሙግቱ ተከሳሽ የሚሆኑ ባለስልጣናት እና ግለሰቦች    

   ትምህርት ሚኒስትር (ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ) ፕሮፌሰሩ በተከሳሽነት የሚያስጠይቃቸው የሚመሩት ተቋም ሂጃብ ከልካይ የሆነ ፖሊሲ እና ህግ በማምንጨቱ ብቻ ሳይሆን አድሏዊ ህግ እና አሰራር እንዲወገድ እና ሁሉንም አካታች በሆነ መልኩ ሁሉም ዜጎች ያለ ልዩነት ትምህርት እንዲያገኙ የማድረግ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ አለመወጣታቸው ተከሳሽ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ይህ ሂጃብ ከልካይ የሆነው መመሪያ እና ፖሊሲያቸውን በየጊዜው በሚዲያ እየወጡ የተከለከለው ኒቃብ እንጂ ሂጃብ አይደለም እያሉ እንደ ጀብድ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመሆኑም በስልታዊ ሙግቱ ተከሳሽ መደረግ ይኖርባቸዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ መሰል የኒቃብ ክልከላ የሚያደርጉ እና ሴት እህቶቻችን ከትምህርት ገበታቸው የሚያፈናቅሉ ከፍተኛ የት/ት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) ፕሬዝዳንቶች በሚፈጽሙት የአድሎ ተግባር እና የመብት ጥሰት በስልታዊ ሙግቱ ተከሳሽ ሊሆኑ ይገባል፡፡

የመብት ጥሰቱ የሚስተዋልባቸው ክልሎች ውስጥ ያሉ የትምህርት ቢሮ ሀላፊዎችም በተመሳሳይ መልኩ ተከሳሽ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ትግራይ ክልል ላይ በሚካሄደው የአክሱም ተማሪዎች የሂጃብ ክልከላ የትምህርት ቢሮ ሀላፊው እንዲሁም የዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ በወረዳ ደረጃ የሚካሄደው የመብት ጥሰቱ በማስቆም ሂደት ጣልቃ ገብተው እርምጃ አለመውሰዳቸው (የወቅቱ የስልጣን ግጭት እንደተጠበቀ ሆኖ) በአግባቡ የሚጠበቅባቸው ሃላፊነት ያህል ጥረት አድርገዋል ወይስ የመብት ጥሰቱ በተዘዋዋሪ የእነርሱም ፍላጎት ነው በሚያስብል መልኩ ዝም ብለው ነው? ወይስ በጣም ቸልተኛ ሆነዋል? የሚለውን በደንብ ተመርምሮ ከምናገኘው መደምደሚያ አንጻር ተከሳሽ ማድረግ ይኖርብናል፡፡

የትምህርት ቤቶች አስተዳዳሪዎች

ከዚህ በፊት ሲስተዋል የቆየው የኒቃብ ክልከላ በአንድ አንድ ከፍተኛ የት/ት ተቋማት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በአጠቃላይ የትምህርት ደረጃ ውስጥ ደግሞ በጥቂት ቦታዎች (ጉንችሬ፣ አክሱም…..ወዘተ) በቅርብ ያስተዋልነው ጉዳይ ነው፡፡ የአክሱም ትምህርት ቤቶች የሂጃብ ክልከላ ለየት የሚያደርገው ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ጸጉራቸው እንኳን እንዲሸፈኑ መከልከሉ ነው፡፡

የትምህርት ተቋማት ለምን ሂጃብ እንደሚከለክሉ ሲጠየቁ ትምህርት ከሀይማኖታዊ ተጽዕኖ ነጻ ሆኖ መካሄድ አለበት በማለት ህገ-መንግስቱ አንቀጽ 90/2 ደንግጓል በማለት መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ድንጋጌ እንደ ፖሊሲ አድሏዊ ተግባር ለመፈጸም በጣም አዛብተው በመተርጎም ስለተጠቀሙት ነው እንጂ ድንጋጌው የሚለው ሀይማኖታዊ ስብከት በማድረግ ወይም የሀይማኖት ተቋም በት/ቤት በማቋቋም ትምህርት ላይ ተጽዕኖ ከማድረግ ነጻ መሆንን እንጂ ትምህርት የሚፈልጉትን ሀይማኖት አልባ እንዲሆኑ ወይም በዚህ ሰበብ ከትምህርት እንዲፈናቀሉ በሚል የተቀረጸ ድንጋጌ አይደለም፡፡

የአክሱም ከተማ ት/ቤቶች ሂጃብ ክልከላ ግን ዋናው ፍላጎቱ አክሱም የተቀደሰች ከተማ ስለሆነች ሙስሊም መስጅድ ሊኖረው አይችልም፣ መቀበሪያ ሊኖረው አይችልም እንዲሁም ማንኛውም እስልምናውን የሚገልጽበት ምልክት ሊኖረው አይችልም የሚለውን ትምክህታዊ ሌጋሲ የማስቀጠል አላማን መሰረት ያደረገ ነው እንጂ የትምህርት ተቋማት ከሀይማኖት ተጽእኖ ነጻ ለማድረግ በሚለው መርህ እንዳልሆነ ሀቅ ነው፡፡

ስለዚህ በዚህ ረገድ በክልከላው ተሳታፊ የሆኑ የት/ት ቤቶች ርዕሳነ መስተዳድር፣ የት/ት ጽ/ቤት ኃላፊዎች ተከሳሾች ሊደረጉ ይገባል፡፡ የሙስሊም ሴት ተማሪዎች በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች የሂጃብ ክልከላ ላይ ከላይ የተገለጹት ይህን ከልካይ ፖሊሲና ህግ አመንጪዎችና አስፈጻሚዎች የሆኑ ተቋማት እና ባለስልጣናትና የስራ ኃላፊዎች ተከሳሽ ማድረግ የሚያስፈልግ ሲሆን የመብት ጥሰቱን እንዲታረም በተለያየ የሀገሪቱ ክፍሎች ምዕመናን እና የጥቃቱ ሰለባዎች ጥያቄ አቅርበውላቸው መፍትሔ መስጠት ያልፈለጉ ወይም ቸልተኛ የሆኑ አስፈጻሚ አካላት እና የስራ ሀላፊዎች አጠር ያለ ዳሰሳ ተደርጎ ከውጤቱ መነሻነት ተጠያቂ የሚሆኑ ካሉ በተከሳሽነት ማካተት ይቻላል፡፡

  • የክሱ ዝርዝር

የክሱ ዝርዝር በዋናነት በ3ት ንዑስ ክፍሎች የሚዳስስ ቢሆን

ሀ.  በጉዳዩ ላይ አግባብነት ያላቸው መብቶች እንዲሁም ብሔራዊ ፣ አህጉራዊ እና አለም አቀፍ ህጎች ላይ ትንተና በመስጠት ለተግባሮቹ ህጋዊ ናቸው በሚል የሚነገሩ ትርክቶች ህጋዊ አለመሆናቸውን ከሰብአዊ መብት ህጎች አንፃር የሚዳሰስበት ክፍል ሲሆን በዚህ መሰረት፡-

  • የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 11፣ 25፣ 27፣ 41/3 እና/4፣ 90 እና መሰል ድንጋጌዎችን ከተግባር ነክ ጉዳዮች እና ከአለም አቀፍ እና አህጉራዊ ህጎች አንፃር መተንተን (ይህ ትንታኔ መኖሩ በክሱ ሂደት በክርክር መልክ ለሚቀርቡ ጉዳዮች ተገቢውን ሙግት ለማቅረብ የሚያግዝ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፡- መንግስት እና ሀይማኖት የተለያዩ ናቸው፣ የኒቃብ ክልከላን ከደህንነት ስጋት ጋር የማያያዝን ፣ ሀይማኖቱ ሂጃብን እንጂ ሌሎች አለባበሶችን አያስገድድም የሚሉ እና ለመሰል ጉዳዮች ከህግ አንፃር መንደርደሪያ ለማቅረብ የሚያግዝ ይሆናል)፣
  • ICCPR- the right to religion, Article 18 (ከነ መገደቢያ ምክንያቶች የሚተነተንበት) , ጠቅላላ ሀሳብ (General Comment) 22
  • ICESCR- The right to Education, Article 13 , ጠቅላላ ሀሳብ (General Comment)  13
  • UNESCO convention against discrimination in education
  • መርሆዎች፡- የእኩልነት መርህ፣ ያለማግለል መርህን

ለ. የመብት ጥሰቱ መቼ እና በምን አይነት ሁኔታ እንደተፈፀመ በዝርዝር ማቅረብ

  • ጥሰቱ የተፈፀመባቸው ቦታዎች በመለየት የተፈፀመውን የመብት ጥሰት ማመላከት
  • ጥሰቱ የተፈፀመባቸው ሁኔታዎችን እና በማን ላይ እንደተፈጸመ ማመላከት

ሐ. በመብት ጥሰቱ ምክንያት የደረሱ ጉዳቶች

  • ትምህርት የማቋረጥ
  • የስነ ልቦና ጉዳቶች ካሉ
  • ሌሎች ጉዳቶች ካሉ
  • የሚጠየቀው ዳኝነት

ሀ. ለመብት ጥሰት ምክንያት የሆኑ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን በመለየት እንዲሻሩ ወይም እንዲሻሻሉ መጠየቅ፤

ለ. ለመብት ጥሰት ምክንያት የሆኑ አሰራሮች ወይም ተቋማዊ አደረጃጀቶች ካሉ በመለየት ማስተካከያ እንዲደረግ መጠየቅ፤

ሐ. ተበዳዮችን ወደነበሩበት ቦታ መመለስ፦ ተማሪዎቹ ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ እንዲወሰን መጠየቅ፤

መ. ለተበዳዮች ህሊና ተስማሚ የሆኑ እርምጃዎች፦ በህዝብ ፊት ይቅርታ እንዲጠየቅ ማድረግ፡፡ እንደተቋምም እንደግለሰብም፣

ሠ. ካሳ፦ ተጎጂዎችን በገንዘብ እና በገንዘብ ለማይተመኑ ጉዳቶች ተገቢውን የካሳ ክፍያ መስጠት፤

ረ. መልሶ ማቋቋም ፦ ተጎጂዎች እንዲያገግሙ ያሚያስችሉ ሳይኮሎጂ እና መሰል ወይም ሌሎች እርምጃዎችን እንዲወሰዱ መጠየቅ፣

ሰ. ሰብዓዊ መብት ጥሰት ዳግም እንደማይከሰት ማረጋገጫ እንዲሰጥ መጠየቅ ፦ ለምሳሌ በስልታዊ የሰብአዊ መብቱ ጥሰት ላይ የተሳተፉ አካላት ከስራ ሀላፊነታቸው እንዲነሱ ወይም የዲሲፕሊን/የእርምት እርምጃዎችን እንዲወሰድባቸው መጠየቅ፡፡

  • ማስረጃዎች

. የሰነድ ማስረጃዎች

  1.  ለጥሰት መነሻ የሆኑ ህጎች/ደንቦች/መመሪያዎች
  2. ጥሰቱን ያባባሱ ደብዳቤዎች/ቃለ ጉባኤዎች/ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች
  3. ጥሰት ለመፈፀም ያገዙ ማስታወቂያዎች/ መግለጫዎች
  4. ጥሰት የተፈፀመባቸው ሰዎች የደረሰባቸው ጉዳት ካለ የሚያሳዩ (ለምሳሌ- የህክምና ማስረጃዎች)

. የሰው ማስረጃዎች

  1. ጥሰት የተፈፀመባቸው ሰዎች
  2. ጥሰት ሲፈፀም የተመለከቱ ሰዎች
  3. ካስፈለገ የአዋቂ ምስክሮች

. ሌሎች ማስረጃዎች

  1. ምስሎች
  2. ቪዲዮዎች

4. ለስልታዊ ሙግቱ አስፈላጊ የሆኑ ባለሙያዎች

ይህን መሰል ከአንድ የዳኝነት ጥያቄ ባለፈ ሀገራዊ እንደምታ ያለውና ተፀዕኖ ፈጣሪ የሆነ ሙግት በርካታ የህግና ሌሎች ሙያተኞችን የሚጠይቅ ነው፡፡ ከሌሎች ሙስሊም ሙያተኞችና ማህበራት የሚያስፈልጉንን የሙያ፣ የቁሳቁስና ሌሎችም ድጋፎችን ከወዲሁ ማፈላለግና በጋራ የምንሰራባቸውን ማዕዘኖች በመለየት ላይ እንገኛለን፡፡

እንደሚታወቀው ማህበራችን የህግ ባለሙያዎች ማህበር እንደመሆኑ በውስጣችን የጥብቅና፣ የዓቃቤ ህገነት፣ የዳኝነት፣ የህግ መምርነትና ሌሎች የህግ ሙያ ዘርፎች ውስጥ ተሰማርተው የሚገኙ የተመዘገቡና ለምዝገባ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ አባላት አሉ፡፡ በየትኛውም የህግ ሙያ ዘርፍ ላይ ተሰማርታችሁ የምትገኙ ይህ መልዕክት የደረሳችሁ ባለሙያዎች በሰነዱ ላይ መካተት አለበት የምትሉት ማሻሻያ፣ ተጨማሪ ሀሳብም ሆነ አዲስ የሙግት ስልትና አቅጣጫ ሊኖር እንደሚችል እንገምታለን፡፡

ከዚህ በላይ የቀረበውን የስልታዊ ሙግት መነሻ ሀሳብ ሰነድና ቀጣይ ስራዎችን በጥብቅና፣ በጥናትና ምርምር፣ በማስረጃ ማጠናቀር፣ በክስና በሌሎች የሰነድ ዝግጅት እንዲሁም በጠቅላላ ባላችሁ የህግ ሙያ ለማገዝ የምትፈልጉ የማህበራችን የተመዘገባችሁ አባላትም ሆነ አባል ያልሆናችሁ ሙስሊም የህግ ባለሙያዎች በዚህ የተከበረ የዲንና የሙያ ኃላፊነት የመወጣት እድል ተጠቃሚ እንድትሆኑ እንጋብዛለን፡፡

ማህበራችን ለዚህ ስልታዊ ሙግት ከሚያስፈልገው ከፍተኛ በጀት አንጻር አብዛኛውን ስራ እንደ አስከአሁኑ የሙያ ሰደቃቸውን ለማውጣት በሚሹ በጎ ፍቃደኛ ባለሙያዎች ነው ለማከናወን ያቀደው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ስራ ጋር ተያይዞ ለሚያስፈልጉ የጽህፈት፣ ህተምና ሌሎች መሳሪያዎች የሚያስፈልገውን ወጪ (Clerical Expenses) ሙሉ ለሙሉ ማህበሩ የሚሸፍን ሲሆን ለወደፊቱ የማህበሩ አቅምና በጀት በፈቀደው ልክ በዚህ ስራ ላይ ለሚሳተፉ ባለሙያዎች የፍርድ ቤትና ሌሎች ተቋማት ጉዞ የውሎ አበል የሚከፍልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት አቅዷል፡፡

በመሆኑም በዚህ አጋጣሚ የማህበራችን መስራች አባልነታችሁን በሙያዊ አስተዋጽዖ መጀመር የምትፈልጉ በጎ ፍቃደኛ ባለሙያዎች ከዚህ በታች በተጠቀሱት የስልክና የኢሜል አድራሻዎች ሙሉ ስምና አድራሻችሁን እንዲሁም በዚህ ስልታዊ ሙግት ስራ ውስጥ ለመስጠት የምትፈልጉትን አገልግሎት አይነት እንዲሁም የጥብቅና ስራ ላይ የተሰማራችሁ ባለሙያዎች የጥብቅና ፍቃዳችሁን ፎቶ ግራፍ እንደትልኩልን በማክበር እንጠይቃለን፡፡

የምዝገባ ጊዜ እስከ ግንቦት 25 ቀን 2017 ነው፡፡

የኢ.ሙ.ህ.ባ.ማ የስልታዊ ሙግት ዲፓርትመንት

አድራሻ፡- ቂርቆስ ክ/ከ አፍሪካ ህብረት ወረድ ብሎ ግደይ ህንጻ 1ኛ ፎቅ ቢሮ ቁጥር 113

ለተጨማሪ መረጃ፣ ስ.ቁ፦ +251983073536 (ለአጭር መልዕክት፣ ለቴሌግራምና ዋትሳፕ መልዕክቶች)

ኢሜል:- emlpa.org@gmail.com.

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *